Ethiopia's Pride

ለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ሰጭዎች የተዘጋጀ የህጋዊ መዋቅር እና አደረጃጀት ጥናት

This document is a review summery / ይህ ፅሁፍ ከሙሉ መረጃው ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው

በቀይ የተቀለመው ክፍል መንግስት ባለው አሰራር ላይ እንዲጨምር የተመረጡ ማሻሻያዎች ናቸው:: የተቀረው ክፍል አሁን ተግባራዊ የሆነውን አሰራር ተግባራዊ እንዲደረግ ይጠይቃል::
_________________________________

መግቢያ፦

ይህ ጥናታዊ ፅሁፍ የተዘጋጀው አዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊና አለም አቀፋዊ ይዘቱን የጠበቀ የመጓጓዣ መዋቅር እንዲኖራት ለማስቻል ነው:: ትኩረት የተሰጠውም የማጓጓዣ አይነት ከ12 ሰዎች በታች የሚጭን አሽከርካሪዎችን ያማከለ ሲሆን፣ ከተጠቀሰው የሰው ብዛት በላይ ለሚጭኑ መኪኖችም ተጨማሪ ማሻሻያዎችን በመጨመር ለወደፊት የሚቀርብ ይሆናል:: በማቀናበር ሂደት ውስጥ ሌሎች የሰለጠኑ ሃገራት የደረሱበትን የአደረጃጀት ተሞክሮ በጥልቀት ለመዳሰስ የተሞከረ ሲሆን ፣ ከሃገራችን ነባራዊና የወደፊት እቅድ ጋርም ለማጣጣም ተሞክሯል::

ለመነሻ ያህል በህዝብ ትራንስፖርት ዘርፉ በኩል ከተማችን ስለምትመራበት የGTP እቅድ አጭር ገለፃ መስጠት ተገቢ ይሆናል:: በዚህ እቅድ ውስጥ ከተካተቱት ነጥቦች ውስጥ ጥቂቱ

1. የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላትን እንደ ህጋዊ አካላት ወይም ድርጅት አደራጅቶ በስራ እንዲሰማሩ ማድረግ
2. በከተማችን ውስጥ የሚገኙትን ሚኒባስ መኪኖች ከመሃል ከተማ አውጥቶ በምትካቸው ከ40 በላይ ሰዎችን የሚጭኑ ባሶችን
ማስገባት
3. በተለምዶ ላዳ ተብለው የሚጠሩትን ነጭና ሰማያዊ የኮንትራት ታክሲዎችን ተመሳሳይ መጠን ባላቸው አዲስና ዘመናዊ መኪኖች
መተካትየሚቀረፀው አደረጃጀት
4. ተጨማሪ የባቡር መሰረተ-ልማቶችንና ፉርጎዎችን መጨመር ይገኙበታል::
እነዚህን እቅዶች ለማሳካት እንዲሁም አዳዲስ አለም አቀፋዊ አሰራሮችን ለማካተት ሲባል በዚህ ጥናት የሚሰጠው አደረጃጀት የሚከተሉትን ነጥቦች ታሳቢ አድርጓል
1. አዲሱ መዋቅር በገበያ ውስጥ የሚገኙትን የትራንስፖርት ሰጭዎች እንዲሁም አዲስ ጀማሪዎችን ባማከለ መልኩ እንዲሰራ ያስችላል
2. የሚቀረፀው አደረጃጀት የአገልግሎት ሰጭዎችን አቅም እና የአፈፃፀም ብቃት ያማክላል
3. ለአደረጃጀት የሚጠቅሙትን ግብአቶች የሃገራችንን ምጣኔ ሃብት በሚያመዛዝን መልኩ ከብዙ ምንጮች እንዲዋቀር ያስችላል
4. አደረጃጀቱ የተለያዩ ተያያዥ ዘርፎች በጥምረት እንዲሰሩ ያስችላል
5. ህግን በጠበቀ መልኩና ተጠያቂነትን ባጎሎበተ መልኩ አሰራር እንዲወጣ ያስችላል
6. የሸማቾችን ወይም የተገልጋዮችን እርካታ ያገናዘበ አወቃቀር ያዘጋጃል
7. አደረጃጀቱ መዋቅርን እንደተከተለ በዘላቂነት መስፋፋት የሚችል ይሆናል
8. የሚተገበረው አደረጃጀት አሁን ሃገሪቱ የምትጠበቅበትን ህግ ወይም መመሪያ መቀየር ሳያስፈልግ ባለው ላይ በመጨመር ብቻ ሁሉን ያማከለ የተሻለ መዋቅር የሚዘረጋ ይሆናል
…………………………………….
ባሁኑ ግዜ በከተማችን ውስጥ ተግባራዊ ሆነው የሚያገለግሉ የታክሲና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ቢኖሩም፣ የሚያስተዳድራቸው የ አፈፃፀም መመሪያ ጥልቀት ስለሚጎለው አተገባበር ላይ ብዥታዎችን እየፈጠረ ይገኛል:: በዚህም ምክንያት ትራንስፖርቴሽን ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እንቅፋት ሆኗል:: ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ጠቅላላ የከተማችንን አደረጃጀት ፈትሾ ተጨማሪ አስታራቂ መመሪያዎችን መቅረፅ አስፈላጊ ይሆናል::

ጥንስሱ ላይ ትራንስፖርቴሽን ዘርፉን ለማዘመን በሚል እሳቤ ከሶስት በላይ የሚሆኑ የግል ድርጅቶች የቀረጥ ነፃ እድል እንዲሰጣቸው የፌደራል መንገዶችና ትራንስፖርት ባለስልጣንን ቢጠይቁም፣ በቂ ጥናት ሳይደረግበት ቅድሚያ ለተሰጣቸው በከተማው ውስጥ እያገለገሉ ለሚገኙት የነጭና ሰማያዊ ታክሲዎች በሩ ክፍት ሆነ:: በዚህም መሰረት በአንድ ቀን ውስጥ ወደ 2100ሺ ሰዎች በፌዴራል መንገዶችና ትራንስፖርት ባለስልጣን አዳራሽ ውስጥ በመሳተፍ ስብሰባ አድርገው መደራጀቱን ሀ ብለው ጀመሩ:: በስብሰባው ላይ የነበሩት ውዥንብሮች ባጭሩ ሲዘረዘሩ፦

1. በአቅማቸው ሊገዙት ስለሚችሉት የመኪና አይነት ግርታ
2. የማህበር አባላት የሚደራጁበት ህጋዊ ድርጅት አይነት
3. የመኪናው ሊብሬ የሚመዘገበው በድርጅቱ ነው ወይስ በባለቤቱ
4. “አሽከርካሪዎቹ የሚከፍሉት የግብር መጠን አተማመንን በተመለከተ የቁርጥ ግብር ሆኖ ይቀራል ወይስ በሜትር ከቆጠረው ላይ እንደ ሌሎች ሪሲት የሚቆርጡ ድርጅቶች ግብር ይከፍላሉ” የሚሉት ይገኙበታል::
……………………………………..
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በፌደራል መንገዶችና ትራንስፖርት ባለስልጣንና በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን መሪነት የተመዘገቡትን ተሳታፊዎች በየአካባቢያቸው ተሸንሽነው በሃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅቶችና በአክሲዮን ማህበራት በችኮላ እንዲደራጁ ተደረገ:: በነዚህ ድርጅቶች ውስጥም ከ 35 እስከ 50 አባላት በየማህበራቱ መመስረቻና መተዳደሪያ ሰነዶች ላይ ስማቸውን በማኖር ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች በበቂ ሁናቴ ባልተረዱበት አካሄድ እንዲሰባሰቡ ሆነ:: በዚህ ሂደት ላይ ዋነኛው መለያ የመኪና መግዛት አቅም ሲሆን፣ ሚኒቫን መግዛት የሚችሉት አባላት በ5 የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ሲካተቱ ባለ በ 4 መጫኛ መኪኖችን መግዛት የሚችሉት ደግሞ በ 20 ድርጅቶች ታቅፈው ገንዘብ ማዋጣት ጀመሩ:: ቆይቶ ከነዚህ ማህበራት በተጨማሪ ባለ4 ሰው የሚጭኑ መኪኖችን አንድ የኤርፖርት ታክሲዎች ማህበር አስገብቶ ስራ ጀምሯል::

የሆነው ሆኖ እነዚህ ድርጅቶች ሲመሰረቱ ጀምሮ ትልቅ የአደረጃጀት እክል አብሯቸው ይጓዝ ነበር፦

1. የተዋቀሩት ማህበራት የህዝብ ስብስብ እንደመሆናቸው መጠን አደረጃጀታቸው የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ እንዲፈታ የሚያስችል ከማድረግ ይልቅ፣ አብዛኛው በሃላፊነታቸው የተወሰኑ ድርጅቶች በመዋቀራቸው፣ ከታክስ አንፃር እንዲሁም አባላት እንዲግባቡና አብረው እንዲሰሩ ከማስቻል አንፃር ደካማ ነው
2. አወቃቀራቸው በአብዛኛው ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበራት ስለሆኑ ድርጅቶቹ ውስጥ አለመግባባት ቢከሰት መንግስት ጣልቃ መግባት ባለመቻሉ ከፍተኛ የሃብት ብክነትን፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲንሰራፋ ምክንያት ሆኗል:: በተጨማሪም መንግስት የሰጠውን የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ ለመገምገም እንዳይችል እክል ሆኗል::
3. በድርጅቱ አመራር ላይ የተቀመጡት አካላት በትምህርት ደረጃ የማይመጥኑ በመሆናቸውና ብቁ በሆነ መስፈርት በግልፅነት የተመረጡ ባለመሆናቸው ድርጅቶቹ ከተመሰረቱ ጀምሮ ህጋዊ የሆነ መዋቅር እንዳያሰናዱ ምክንያት ሆኗል
4. ድርጅቶቹ የተበደሩበት ባንክ የሚደርስበትን የስጋት መጠን ለመቀነስ ብድሩን የሰጠው በተዋቀሩት ድርጅቶች ስር በመሆኑ የመኪኖቹ ሊብሬ በድርጅቱ የተያዘ ነው:: በመሆኑም አባላት በእጃቸው ላይ እንደለመዱት ንብረት ባለመኖሩ ከፍተኛ አለመተማመን እንዲፈጠር በር ከፍቷል:: ስለዚህ ሃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ድርጅቶች ገቢያቸውን ወደድርጅቱ የባንክ አካውንት ማስገባት ቢኖርባቸውም ህገወጥ በሆነ አሰራር ቀጥታ ወደኪሳቸው እንዲጨምሩ ምክንያት ሆኗል
5. የንግድ ህጉ እንደሚያዘው ከሆነ ድርጅቶች የተለየ ፈቃድ ወይም የቀረጥ ማበረታቻ ካልተሰጣቸው በቀር፣ ሃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ድርጅቶች ከ500,000 ብር በላይ በአመት ገቢ የሚያስገቡ ከሆነ ሪሲት መቁረጥና በዓመት መጨረሻ የትርፍ ክፍፍል ማድረግ ሲገባቸው፣ ይህ አሰራር ፈፅሞ ተሽሮ ህገወጥ የሆነ አሰራር እንዲከተሉ እድል ተፈጥሯል
6. ድርጅቶቹ በአመት መጨረሻ በገቢዎች ኦዲት ስለማይደረጉ መኪኖች ላይ ከሚለጠፈው ማስታወቂያ የሚገባው በሚልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ጠያቂ በሌለበት መልኩ ለሙስና እየዋለ ይገኛል
7. የመኪና ግዥ ላይ ግልፅነት የሌለበት በመሆኑ ከፍተኛ የሙስና ኔትወርክ ፈጥሯል::
8. ሊብሬው በድርጅት የተያዘን መኪና የድርጅትን ካፒታል ሳያሳድጉ ህገወጥ በሆነ መልኩ ከባለቤት ወደባለቤት እንዲተላለፍ በር ተከፍቷል::
9. ድርጅቶቹ ጥልቅ የሆነ መተዳደሪያ ደንብ ስለሌላቸው አባላት ስራ አስኪያጆችን በሃላፊነት እንዲሰሩ ለማድረግ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሮባቸዋል
…………………………………….
በሌላ በኩል፣ ተገዝተው ወደ አገልግሎት ላይ የዋሉት መኪኖች የወደፊት ህልውናቸው የሚዳኘው በሚያገኙት የተሟላ ጥገናና በቂ መለዋወጫ መሆኑ ግልፅ ነው:: ይህንን ያህል ወጭ ወጥቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ መኪኖች ሲገዙም በመለዋወጫ ላይና በጥገና ዋጋ ላይ ቢያንስ የባንክ እዳ ሙሉ በሙሉ እስከሚሸፈንበት ወቅት በተጋነነ ሁናቴ እንዳይንር ሰፊ ድርድር የሚጠይቅ ነው:: ይሁንና በተለያየ ግዜአት ማህበራቶቹን ጠምዝዞ የያዘው ክርክር ኦሪጂናል የጥገና እቃ አስመጭው ድርጅት አንድ ብቻ እንዲሆን በመደረጉ መኪኖቹን የሚያስተዳድሩት አባላት ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸው ነው:: አንዳንዶቹ ሲበላሽ ሞዲፊክ ለማሰራት ሲገደዱ በአብዛኛው ደግሞ ስራን በሰፊው አቀላጥፎ ከመስራት ይልቅ ቀድሞውኑ የመኪናቸውን እድሜ ለማራዘም አጭር መንገድ በብዙ ገንዘብ ወደሚከፈልበት የድርድር አሰራር እንዲቀላቀሉ አድርጓቸዋል:: መንግስት ይህንን ያህል ትልቅ ቁጥር ያለው የመኪና ክምችት ለትራንስፖርት ሲያሰማራ ሊታሰቡ ከሚገባቸው አንኳር ነጥቦች ውስጥ የሚከተሉት ይገኝበታል

  • የመኪና አቅርቦቱ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም ማዳረስ እንደሚቻል ማረጋገጥ
  • የሚገዙት መኪኖች በቂ ጥገናና መለዋወጫ በሃገሪቱ እንዲገኝ ማስተማመን
  • መኪኖች ሲቀየሩ ነባሮቹን የማስወጣት ስራ በጥልቀት መስራት
  • የመኪኖቹ ብቃት ለረዥም ዓመት እንደሚያገለግል መገምገም

በአዲስ አበባ ስለሚተገበረው የትራንስፖርቴሽን አደረጃጀት ችግሮች ጥቂት ካልን ወደ መፍትሄው ስንመጣ ከ12 ሰዎች በታች ለሚጭኑ የትራንስፖርቴሽን አይነቶች ሶስት አይነት የአገልግሎት ክፍፍሎሽ በተለያዩ የሰለጠኑ ሃገራት ተተግብረው ስራ ላይ ይገኛሉ :: ይዘታቸውም ከሃገራችን አሰራር ጋር በመጠኑ ስለሚጣጣም በመሰረታዊነት ወስደን ጥቂት ማሻሻያዎችን ልናደርግበት እንችላለን::
___________________________________________

የአደረጃጀት መፍትሄ፦

ከ 12 ሰዎች በታች ለሚጭኑ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች የሚከተሉት ሶስት መሰረታዊ አደረጃጀቶች ይቀርባሉ

1. ቋሚ የታክሲ አገልግሎት
2. ሰውን ከመኪና ጋር ወይም መኪናን ብቻ የማከራየት (የመቅጠር) አገልግሎት
3. ልዩ አጋዥ ሃይል የታክሲ አገልግሎት ናቸው::
………………………………………

1. ቋሚ የታክሲ አገልግሎት

በዚህ የታክሲ አገልግሎት ስር ሊጠቃለሉ የሚችሉ አካላት፣ ሰማያዊ በነጭ ላዳ ታክሲዎች እና የሜትር ታክሲዎች ናቸው:: እነዚህ የትራንስፖርት አይነቶች ከተቀሩት ሁለት ክፍሎች የሚለዩት፣ መንገድ ላይ ተሳፋሪን የማንሳት ወይም የኮንትራት ታክሲ ተራ የሚያዝበት ቦታዎች ላይ መቆም ፈቃድ (የታክሲ ታርጋ) ስለሚሰጣቸው ይሆናል:: በአሜሪካ ይህ ፈቃድ ሜዳልያ (Medallion) ተብሎ ይጠራል:: እዚህ ጋር ልንገነዘብ የሚገባው የኦፐሬተር ፈቃድ የሚሰጠው አካል የመኪናው ባለቤት ሳይሆን መኪናውን እያሽከረከረ የታክሲ አገልግሎት ለሚሰጥ ግለሰብ ነው:: የመኪናው ብቃት የሚረጋገጠው በአመቱ መጨረሻ በሚደረገው የቦሎ ምርመራና የታክሲ ታርጋ ለመቀበል የሚቀመጡት መስፈርቶች ውስጥ ይጠቃለላል::
የኦፐሬተር ፈቃድ ያስፈለገበትም ምክንያቶች እንደሚከተለው ይዘረዘራሉ:

  • አለም አቀፋዊ የታክሲ አገልግሎት አሰጣጥ በከተማችን እንዲኖር የታክሲ አሽከርካሪ ማሟላት የሚገባውን መስፈርቶች ለመፈተሽ
  • አገልግሎት ሰጭው ጥልቅ የሆነ ስልጠና ተሰጥቶች የብቃት ማረጋገጫ ስለሚያስፈልገው (ስለ አደጋ ግዜ ምላሾች፣ ለአካለ ስንኩላን ተገቢ አገልግሎት ስለመስጠት፣ ታማሚን በአግባቡ ስለማጓጓዝ…)
  • የአሽከርካሪውን ያለፈ ታሪክ አጣርቶ ከወንጀል ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ
  • ከመንገድ ላይ ወይም የታክሲ ተራ ከሚያዝበት አካባቢ ተሳፋሪን ማንሳት እንዲችሉ የተለየ ፈቃድ ለመስጠት የአሽከርካሪውን ብቃት ለማረጋገጥ

በአንፃሩ የታክሲ ታርጋ ወይም ሜዳልያ የመኪናውን ብቃት በሚከተሉት መስፈርቶች ሊተምን ይችላል::

  • የውስጣዊ ካሜራ፣ የአደጋ ግዜ መጥሪያ ቁልፍ፣ ጂ ፒ ኤስ እንዲሁም የ ኦፐሬተር መታወቂያ
  • የሚቀመጥበት ስፍራ መኪናው እንዳሰናዳ ማረጋገጥ
  • የቦሎ ምርመራ መስፈርቶችን ሙሉ በሙሉ ማሟላቱን ማረጋገጥ
  • ለታክሲ የተፈቀደለት ቀለም እንዳለው ማረጋገጥ
  • የሚፈቀደውን የመኪና አይነት ለሚያሟሉ አካላት የሜትር መቁጠሪያ እንዳለው ማረጋገጥ

በከተማችን ለታክሲ የሚፈቀዱ የመኪና አይነቶች እንደሚከተለው ይቀመጣሉ
i. ደረጃ 1 – የምርት ዘመኑ አምስት ዓመት ያልሞላው መኪና
ii. ደረጃ 2 – የምርት ዘመኑ ከአምስት እስከ አስር ዓመት የሆነው
iii. ደረጃ 3 – የምርት ዘመኑ ከአስር እስከ አስራ አምስት ዓመት የሆነው

አሁን በገበያ ላይ የሚገኙ ነጭና ሰማያዊ መኪኖች ከላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች ባያሟሉም መኪና እስኪቀይሩና ሜትር እስኪገጥሙ ድረስ የዕፎይታ ግዜ እንዲሰጣቸው ይደረጋል:: እስከዚያው ድረስም በሚከተሉት አደረጃጀቶች ተዋቅረው ሊሰሩ ይችላሉ::

ባጠቃላይ ቋሚ የታክሲ አገልግሎቶች በሁለት መልኩ ሊደራጁ ይችላሉ:-

I. በታክሲ ድርጅት የተያዘ መኪና፦ የመኪናው ባለቤትነት ወይም የመኪናው ሊብሬ በአንድ ድርጅት ስር ሆኖ አሽከርካሪው እንደተቀጣሪ የሚሰራበት አደረጃጀት ነው (የድርጅት ባለድርሻም ሆነ የውጭ አካል መኪናውን ሲሰራበት እንደተቀጣሪ ይቆጠራል):: የሚያሽከረክረው አካል ኦፐሬተር ፈቃድና የግል ቲን ቁጥር እንዲያወጣ ይደረጋል:: ምሳሌ: በከተማችን የተደራጁት የሜትር ታክሲዎች
የዚህ አይነት አደረጃጀት በኀ/የተ/የግ/ማ ወይም በአክሲዎን ማህበር ሆኖ የትራንስፖርቴሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍን አካቶ የሚመሰረት ሲሆን፣ መኪናውን የያዘው ድርጅትና የታክሲው አሽከርካሪ (ኦፐሬተር) በተናጠል ግብር የሚከፍሉ ይሆናል::

በዚህም መሰረት መኪናውን የያዘው ድርጅት የሚከተሉትን ተግባራት ያከናውናል

  • ድርጅቱ ሙሉ መለዮ የያዘ መኪና ለኦፐሬተር አሽከርካሪዎች ያቀርባል፣ ጥገናውንም ያከናውናል
  •  አባል አሽከርካሪዎች ስራ እንዲያገኙ ስለሚሰጠው አገልግሎት ማስታወቂያ ይሰራል
  •  ህግና ደንብን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት አሰጣጥን የተሳለጠ ለማድረግ የድርጅት መመሪያዎችን ያወጣል እንዲሁም ያስፈፅማል
  •  የተለያዩ የታክሲና የክፍያ ቴክኖሎጂዎችን ለአሽከርካሪዎች በግል ወይም በፓርትነርሽፕ ያቀርባ
  •  የአገልግሎት ጥራትን ለማጎልበት ለድርጅቱ ኦፐሬተሮች ስልጠናን ያመቻቻል
  •  በድርጅቱ ስር የሚገኙት መኪኖች የግልና የሶስተኛ ወገን ሙሉ ኢንሹራንስ እንዳላቸው ማረጋገጥ ይኖርበታል
  •  ለሚሰጣቸው ጥቅሞችና ላቀረበው መኪና የአገልግሎት ክፍያ በየወሩ በሪሲት ያወራርዳ
  •  የሚጠበቅበትን ግብር ከመንግስት ጋር በወቅቱ ያወራርዳል
  •  ለድርጅት ባለድርሻ አካላት የትርፍ ክፍፍል በአመቱ መጨረሻ ያደርጋል

የድርጅት ተቀጣሪ የታክሲ ኦፐሬተሮች የሚከተሉትን ተግባራት ይፈፅማሉ

  •  የኦፐሬተር ፈቃድንና ህጋዊ ሰነዶችን አሟልቶ ይገኛል
  •  የቁርጥ ግብር የሚከፈልበት የግል ቲን ቁጥር ያወጣል (የቁርጥ ግብር እድል የሚሰጠው ለመኪና ባለቤት ድርጅት ሳይሆን ለታክሲ አሽከርካሪው ነው:: ምክንያቱም አቅራቢ ድርጅቱ ገቢው ከ500,000 ብር በላይ ስለሆነ ህግን ሳያዛቡ የቁርጥ ግብር መተግበር የሚቻለው በተናጥል የወጣ ቲን ቁጥር ላይ ነው)
  •  በየወሩ የአገልግሎት ክፍያ ለድርጅቱ ይከፍላል:: የድርጅቱ ባለድርሻም ከሆነ በዓመቱ መጨረሻ የትርፍ ክፍፍል ውስጥ ተሳታፊ ይሆናል

II. በግለሰብ ባለቤትነት የተያዘ መኪና፦ ግለሰቦች የራሳቸውን መኪና ወደ ታክሲነት ከቀየሩ በኋላ በየደረጃቸው 1 ቁጥር ታርጋ አውጥተው በአንድ ድርጅት ስር በመታቀፍ የሚሰሩበት አሰራር ነው:: እነዚህ ታክሲዎች ቁጥር 1 ታርጋ እንዲሰጣቸው በአክሲዎን ድርጅት ስር ሊብሬ ሳያስይዙ ድርሻ በመግዛት መታቀፍ ይችላሉ:: አሽከርካሪዎቹም የኦፐሬተር ፈቃድና የታክስ ቲን ቁጥር እንዲያወጡ ይደረጋል::
ለምሳሌ: ሰማያዊና ነጭ ላዳ ታክሲዎችን በተለያዩ አክሲዎን ድርጅቶች አደራጅቶ እንዲሰሩ ማስቻል ነው::

በዚህም መሰረት መኪናውን የያዘው ድርጅት የሚከተሉትን ተግባራት ያከናውናል

  •  የድርጅት መለዮ እና የመኪና ቀለም ያወጣል እንዲሁም የመለዮውን ህልውና ያስጠብቃል
  •  የድርጅቱን መለዮ የያዙትን አባላት በጥልቀት ይመዘግባል፤ አሽከርካሪዎቹም ተገቢውን የህግ ሰነድ ማሟላታቸውን ያረጋግጣል
  •  አባል አሽከርካሪዎች ስራ እንዲያገኙ ስለሚሰጠው አገልግሎት ማስታወቂያ ይሰራል
  •  ህግና ደንብን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት አሰጣጥን የተሳለጠ ለማድረግ የድርጅት መመሪያዎችን ያወጣል እንዲሁም ያስፈፅማል
  •  የአሽከርካሪ መቅጫ ደንቦችን ያወጣል እንዲሁም ያስፈፅማል
  •  ተመዝጋቢ መኪኖች የግልና የሶስተኛ ወገን ሙሉ ኢንሹራንስ እንዳላቸው ማረጋገጥ ይኖርበታል
  •  የተለያዩ የታክሲና የክፍያ ቴክኖሎጂዎችን ለአሽከርካሪዎች ያቀርባል
  •  የአገልግሎት ጥራትን ለማጎልበት ለድርጅቱ ኦፐሬተሮች ስልጠናን ያመቻቻል
  •  ለሚሰጣቸው ጥቅሞች የአገልግሎት ክፍያ በየወሩ በሪሲት ያወራርዳል
  •  የሚጠበቅበትን ግብር ከመንግስት ጋር በወቅቱ ያወራርዳል
  •  ለድርጅት ባለድርሻ አካላት የትርፍ ክፍፍል በዓመቱ መጨረሻ ያደርጋል

በዚህ ድርጅት ውስጥ የተደራጁ የታክሲ ኦፐሬተሮች የሚከተሉትን ተግባራት ይፈፅማሉ

  •  የኦፐሬተር ፈቃድንና ህጋዊ ሰነዶችን አሟልቶ ይገኛል
  •  የቁርጥ ግብር የሚከፈልበት የግል ቲን ቁጥር ያወጣል (የቁርጥ ግብር እድል የሚሰጠው ለመኪና ባለቤት ሳይሆን ለታክሲ አሽከርካሪው ነው)
  •  በየወሩ የአገልግሎት ክፍያ ለድርጅቱ ይከፍላል:: የድርጅቱ ባለድርሻም ከሆነ በአመቱ መጨረሻ የትርፍ ክፍፍል ውስጥ ተሳታፊ ይሆናል

የዚህ አይነት አደረጃጀት የመጠይቀው አክሲዎን ማህበር ሲሆን፣ ምክንያቱም

  •  የመኪናው ንብረትነት በተናጥል ስለተያዘ በአባላት መሃከል አለመስማማት ቢከሰት ወይም የህግ ጥሰት ቢፈፀም መንግስት ጣልቃ ገብቶ ለማስተካከል እንዲችል
  •  መስራቾችን ብቻ ሳይሆን ባለድርሻ አባላትን ተጠያቂ በሚያደርግ መልኩ ውል ማሰናዳት ስለሚቻል
  •  የህዝብ ማህበር እንደመሆኑ መጠን የህዝብን ጥያቄ ለማስተናገድ ከሌሎች አደረጃጀቶች በይበልጥ የሚያመች በመሆኑ
  •  አባላት እንደ አቅማቸው የፈለጉትን አይነት መኪና በተናጠል መግዛት እንዲችሉ ስለሚረዳ
  •  ብዛት ያላቸውን አሽከርካሪዎች ማቀፍ ስለሚችል የአገልግሎት ክፍያን ለመቀነስ ይረዳል

…………………………………………….

2. ሰውን ከመኪና ጋር ወይም መኪናን ብቻ የማከራየት (የመቅጠር) አገልግሎት

በዚህ የንግድ ስራ ለመሰማራት የ ኮድ 3 ታርጋና የኪራይ አገልግሎት የሚል የንግድ ፈቃድ ማውጣት ተገቢ ነው:: በተጨማሪም የመኪናው ሊብሬ ላይ ኪራይ የሚል ፈቃድ ይኖርበታል:: በዚህ መሰረት ባለንብረቶች ወይም የኪራይ ድርጅቶች መኪናቸውን ከ አሽከርካሪ ጋር ወይም ያለ አሽከርካሪ ለአጭር ግዜ ወይም ለረጅም ግዜ ማከራየት ይችላሉ ማለት ነው:: በተጨማሪም ክፍያ ለመሰብሰብ ኪሜ. ን ያማከለ የመመተሪያ መንገድ ሊከተሉ ይችላሉ::

ይህንን ፈቃድ የያዙ አገልግሎት ሰጭዎች ከታክሲ የሚለዩበት ዋነኛ ምክንያት

i. የኦፐሬተርነት ፈቃድ እና 1 ቁጥር ታርጋ (Medallion) ስለማይሰጣቸው ፣ በቴክኖሎጂ ታግዞ ተሳፋሪ ካልጠራቸው በስተቀር ከመንገድ ላይ ወይም ታክሲ ተራ ከሚያዝበት አካባቢ ተጓዥ ማንሳት አይችሉም
ii. የድርጅታቸውን መለዮ የመኪናው አካል ላይ መለጠፍ አይችሉም
iii. መኪናቸው ላይ የሚገኙበትን ስልክ ቁጥር መለጠፍ አይችሉም
iv. ተጠቃሚ ያለአሽከርካሪ በራሱ መኪናቸውን ሊጠቀምባቸው ይችላል
v. ለታክሲ የተሰጠን ቢጫ ቀለም አይጠቀሙም

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለንብረቶች ከትራንስፖርት ማገናኛ ቴክኖሎጂ ድርጅት ጋር ባላቸው ውል መሰረት በቴክኖሎጂ ታግዘው የአጭርና የረዥም ግዜና ርቀት አገልግሎት መስጠት ይችላሉ:: ቀድሞውንም የኮድ 3 ታርጋ አውጥቶ ለመንቀሳቀስ የንግድ ፈቃድ የሚያስፈልግ በመሆኑ እነዚህን አንድና ከ አንድ በላይ መኪኖች ያቀፈ ድርጅት መልሶ በሌላ ማደራጀት አስፈላጊ አይሆንም::

በዚህ የስራ ዘርፍ ለመሰማራት ባለንብረቶች የሚከተሉትን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል

  •  በየዓመቱ የቦሎ ምርመራ ብቃት ባለም መልኩ ያለፈ መኪና ማቅረብ
  •  ኢንሹራንስን በተመለከተ የግልና የሶስተኛ ወገን ሙሉ ኢንሹራንስ እንዲኖራቸው ይደረጋል
  •  የመኪና አቅራቢው የኪራይ አገልግሎት ለመስጠት የንግድ ፈቃድ ሊኖረው ይገባል
  •  የመኪና አቅራቢው ዓመታዊ ገቢ ከ 500,000 ብር በላይ ከሆነ የሚጠበቅበትን ግብር ከመንግስት ጋር ማወራረድ ይጠበቅበታል
  •  ተቀጣሪ አሽከርካሪ ግብር ለማወራረድ ቲን ቁጥር ማውጣት ይጠበቅበታል:: ከቀጣሪው ድርጅት ጋር ውል ካለው ደግሞ ከደሞዙ ላይ የገቢ ግብር የሚታሰብበት ይሆናል
  •  በድርጅቶች ስር የሚገኙ መኪኖች ለተፈቀደላቸው ስራ ብቻ መዋላቸውን ያረጋግጣል
  •  በድርጅቱ ስር ለሚገኙት መኪኖችና አሽከርካሪዎች ህግን በጠበቀ መልኩ ደንብ ያወጣል እንዲሁም ያስፈፅማል
  •  በስሩ ለሚገኙ አሽከርካሪዎች የተለያዩ የ ብቃት ማጎልበቻ ስልጠናዎችን ያሰናዳል

……………………………………..

3. ልዩ አጋዥ ሃይል የታክሲ አገልግሎት

የዚህ አይነት የታክሲ አይነቶች የከተማው አስተዳደር የትራንስፖርት እጥረትን ለማቃለል ውስን በሆነ መልኩ የሚሰጠው ፈቃድን ያጠቃልላል:: አሰራራቸውም የተወሰነ ክልሎችን ወይም መስመሮችን ለመሸፈን ወጥ በሆነ ታሪፍ እንዲሰሩ የሚያስገድድ ነው:: ለምሳሌ የኤርፖርት ሻትል አገልግሎትና የሆቴል ታክሲዎች ሊሆኑ ይችላሉ:: የዚህ ዘርፍ አሰራር ከትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር በሚደረግ ውል የሚመሰረት ሲሆን፣ የውሉ ይዘት እንደ አስፈላጊኒቱ ሊዘጋጅ ይችላል::

Share:

More Posts

2016 E.C. New Year Message from our CEO

የራይድ ዋና ስራ አስፈፃሚ መልዕክት:-

እንኳን ለ2016 ዓ.ም አዲስ ዓመት አደረሳችሁ:: መጭው ዓመት በሃገራችን የሰላም- የፍቅር እና የበረከት አመት እንዲሆን በመላው የራይድ ቤተሰብ ስም እየተመኘው- ቤተሰባዊ ወዳጅነታችንን የምናጠናክርበት እንዲሁም በቀናነት የምንተሳሰብበት ዘመን እንሚሆን እምነቴ ነው:: ራይድ የሁላችንም ነው! ስለሆነም- በመጭው ዓመት አገልግሎታችንን ሙሉ ለሙሉ ሰው ተኮር በማድረግ በአለም ተወዳዳሪ የሆነና የአፍሪካ ኩራት የሆነ ጠንካራ ድርጅት በጋራ እንደምንገነባ እተማመናለሁ:: መልካም በዓል ከእነቤተሰብዎ እመኛለሁ::

RIDE Company Profile

Hybrid Designs PLC is a revolutionary Mobility technology company that aspires to implement simple, practical, and efficient mobility systems in Africa. Our

Send Us A Message

Scroll to Top